ስሙኝማ…አንዱ የቅርብ የጓደኛውን የወደፊት ግራ ጎን “ጎሪላ ዋርፌር በሚሉት አይነት ለራሱ በማድረጉ ሀይለኛ ፍጥጫ ተከስቶ ወዳጆች ነገሮች ወደ መጥፎ ደረጃ እንዳይደርሱ እየሞከሩ ነው ሲባል ሰማን፡፡ ነገርዬው “ላቭ ኢዝ ብላይንድ!” አይነት ሰይሆን ገንዘብ ቢጤ አለበት መሰለኝ፣ ባለገንዘቡ ማንኛቸው እንደሆነ እንጃ እንጂ! ዘንድሮ መቼም ገንዘብ የማያደርገን ነገር የለም!  ዘንድሮ፣ ፉክክሩም የጉድ ነው!

ጓደኛውም የሆነ “ሁሉም ምቹ፣ ሁሉም ዝግጁ!” የሆነበት ቦታ በማይታይ ፓራሹትም ዘልሎ ይሁን ሰርስሮ ይገባና ፈረንካውን አግኝቶ መኪና ቢጤ ይገዛል፡፡ መቼም ዘንድሮ የሆነች መኪና ይዞ ከተማ ውስጥ ሲያሽከርክሩ በ’ፒፕሉ’ ለመታየት ያለው እሽቅድምድም ዶናልድ ትረምፕ ሀገር ለመሄድ ካለው እሽቅድምድም ባይበልጥ ነው፡፡   “እሱ የገዛትን ቪትስ ገዝቼማ ዐይኑን ባላቀላው ሞቻታለሁ!” አይነት ፉከራ ይሁን ፉክክር የስንቱን የአንድ ኪሎ ምስር አራት መቶ ብር መግባት ዳምጠው የተመላለሰበት ያስመለውን አንጀቱን እያቆሰለው እንደሆነ ቤቱ ይቁጠረው፡፡  “ሳይችግር ጤፍ ብድር” ማለት ይሄኔ አይደል! ግዴላችሁም… የዛኛው ሰው ወርዶ ዘጭ ማለት የእኛን የተመናመነች መሶብ ላይሞላት ለጨጓራ ይታሰብበትማ! አንድ ጣሳ ዱቄት ወተት እኮ አምስት ሺህ ምናምን የገባበት  ዘመን ነው! እንደምንሰማው ከሆነ በስጋ ዘዶ በልብ ጓደኞች መካከል መፈነጋገል በዝቷል ነው የሚባለው፡፡ 

“አሁን እሱም ሰው ሆኖ አለፈለትና ስልክ እንኳን አላነሳ ይበል!” አነሳ ይበል!  ምን አለ በሉኝ…በአራት እግሩ በዳዴ እየዳኸ እንዲለምነኝ ካላደረግሁትማ ሰው አትበሉኝ!” የምር ግን ግርም አይላችሁም…ሲያልፍለን ወይም ያለፈልን ሲመስለን ትናትንና የትናንት ወዳጆችን የምንረሳው ሉሲፈር ምን ሹክ እያለን ነው! “ምን በወጣህ ነው አሁንም ድራፍት ከሚባል ወንዝ ካልተላቀቁት ጋር አብረህ የምትታየው! ብሎክሳይሆነ ዲለተ አደርጋቸው! ያሳደገውን ድራፍትን “ወንዝ…” ሲልበት “እምዬ ድራፍትን፣ የክፉ ቀኔንማ እንዲህ ማለት አትችልም!” ማለት ቢያቅት እንኳን “ድንቄም መካሪ!” ብሎ ዘወር ማለት ይቻላል እኮ!

እኔ የምለው..፣ እንግዲሀ ጨዋታም አይደል… እንዲህ አይነት ነገሮች፣ ማለትም ዘመድንም ሆነ ወዳጅን “በዳዴ የማስኬድ…” ፉከራ  በወጣቱ አካባቢ በርከት ያሉ ናቸው የሚባለው እውነት ነው እንዴ! ወይስ አልአሀራም ‘እንደለመደው’ ያወራው ነው! (ለ”ጠቅላላ እውቀት ያህል…በፊት ጊዜ አሁን “ሀሰት ዜናዎች፣” የምንላቸውን በማሰራጨት በቁጥር አንድ ጣታችንን የምንቀስርበት እሱ ስለነበረ ነው! ይቺንም ክብራችን ነኩ ብለው ለጸጥታው ምክር ቤት አቤት እንዳይሉ!)

እናማ…”ቆይ የተወለደባትን ቀን ባላስረግመው!” “ምን አለች በሉኝ፣ ጨርቋን ጥላ እንድትሄድ ባለደርጋት!” አይነት ነገሮች አሪፍ ባይሆኑም ነገርዬው ግን እግራችንን ከሰባት መቶ ሀምሳ ብር ጫማ  ወደ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ጫማ ከማሸጋገር የማታልፍ ትንሽዬ ፍራንክ ቢጤ፣ ከዕቁብ ጸሀፊነት እምብዛም የማታልፍ ስልጣን ቢጤ ስናገኝ ትናትንና የትናንት ወዳጆችን መርሳት የለየለት ቅሽምና ነው፡፡ (እኔ የምለው… ያቺ “ስልጣን የዛፍ ላይ እንቀልፍ ነች የምትባለው ነገር፣ ጥቅሷ…ትቅስ ባትሆንም ጥቅስ እንበላትና…ከሼክስፒር ነው ወይስ ስሙን ከረሳነው የሩስያ ደራሲ የተወሰደች! ዘንድሮ ስትባላ የማንሰማው ጥቅስ መሆን ነበረባት በሚል ነው፡፡)

እናማ…ተራ ፉክክር አሳስቆ ወሳጅ የሚወስድ አይመስላችሁም!

“በእሷ ቤት ባለመኪና ቦይፍሬንድ ያዘችና እንዴት፣ እንዴት እንደሚያደርጋት ብታዩ! ያውም ቪተዝም በአቅሟ መኪና ሆነችና! እኛ እኮ ከፈለግን ቪኤይቱን ማሰለፍ እንችላለን!” (እዚህ ላይ “በህግ አምላክ!” እንበል እንዴ! አሀ…ሀገሩ ቪትዝ በቪትዝ ሆኖ የስንቱ እርግማን ይቻላል! “የጫማቸው ሶል እንደ ሰፈር አሽሙረኛ ጥግ ከጥግ እያሾፈ አፍ አለን ብለው ቪትዝ ላይ ከድ ይይዛሉ!” ሊባል ይችላላ! )

አንድ ጊዜ ቆይቷል ፒያሳ አካባቢ የሆነ ነው፡፡ እናላችሁ… እሱዬው የሆነች ቮልስዋገን ይዞ በአጠገቡ ሁለት የፒያሳ ጄነፊር ሎፔዞች ያልፋሉ፡፡ እናማ… መቼ ባለመኪናም አይደል፣ ክላክሱን ያጮህና እንዲገቡ ምልክት ይሰጣቸዋል! ይሄኔ አንደኛዋ ምን ብትል ጥሩ ነው… “ያውም በቮልስ!”  አያምጣው ነው እኮ!…አንድ ሰሞን አቶዝ የምትባል መኪና መጣችና እነእሱዬዎች ለእንትናዬዎቻቸው እየገዙ ይሰጡ ጀበር፡፡ እናማ፣ አቶዝ በታሪክም ‘ገድሏ’ እንዳይጠፋ ነው መሰለኝ ስንኝ ሁሉ ተቋጥሮላት ነበር! (ለህትመት የማይመች ሆነና ነው!)

ምን መሰላችሁ… ባለቪትዟን “ጭራ ላማስበቀል” ባለቪኤይቶችን ‘አደን’ ሲኬድ  መንገድዬው አልጋ በአልጋ ላይሆን ይችላል ለማለት ያህል ነው!


Discover more from Ephrem's ink

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Leave a Reply

Discover more from Ephrem's ink

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading